ዘጠና ታራሚዎች ከጋምቤላ ማረሚያ ቤት አመለጡ

This image has an empty alt attribute; its file name is %E1%8B%98%E1%8C%A0%E1%8A%93-200x113.jpg

በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ትላንት በተቀሰቀሰ ብጥብጥ 90 ታራሚዎች ማምለጣቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኮት ሜንታፕ ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናገሩ። ታራሚዎቹ ያመለጡት በአጥር ዘልለው ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ማረሚያ ቤት ብጥብጡ የተነሳው ትላንት ረፋድ ላይ በሁለት ታራሚዎች መካከል በተፈጠረ የግል ጠብ ምክንያት መሆኑን ከንቲባ ኮት ሜንታፕ ገልጸዋል። ሁለቱ ታራሚዎች ውኃ በጀሪካን ሲቀዱ መጋጨታቸውን የሚናገሩት አቶ ኮት ጠቡ የብሔር መልክ ከያዘ በኋላ ወደ ብጥብጥ ተቀይሯል ብለዋል። የኑዌር እና አኙዋ ጎሳ አባላት ጎራ ለይተው የተሳተፉበት ይሄው ግጭት ለ90 ታራሚዎች ማምለጥ ምክንያት መሆኑንም ከንቲባው አስረድተዋል።

ግጭቱ በተነሳበት ወቅት ከተማው ላይ ተኩስ ይሰማ እንደነበር አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። ማረሚያ ቤቱን እንደሚያውቀው የገለጸው ይሄው ነዋሪ አመለጡ የተባሉት 90 ሰዎች ከጠቅላላው የማረሚያ ቤቱ ታራሚዎች አንጻር ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል።

ያመለጡትን ታራሚዎች ለማስመለስ እና በቁጥጥር ስር ለማዋል የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ዘመቻ መጀመራቸውን የጋምቤላ ከንቲባ አስታውቀዋል። አቶ ኮት ካመለጡት አንዳንዶቹ ወደ ማረሚያ ቤቱ መመለሳቸውን ቢገልጹም ትክክለኛ ቁጥራቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ከንቲባው በትላንትናው የጋምቤላ ማረሚያ ቤት ብጥብጥ «የተጎዳ ሰው የለም» ብለዋል።

(ዘገባ፦ ሰለሞን ሙጬ – ከአዲስ አበባ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *