የኢሕአዴግ ምክር ቤት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን እና ያለፉትን ወራት የእቅድ አፈፃፀም በጥልቀት ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን እና ያለፉትን ወራት የእቅድ አፈፃፀም በጥልቀት ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሚያዚያ 7 – 8 /2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱ ያለበትን ደረጃና የተከናወኑ የፖለቲካና የድርጅት ስራዎችን አፈፃፀም ገምግሟል። 
ባለፈው አንድ አመት በተለይም 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ከተካሄደበት መስከረም ወር ጀምሮ የጉባዔውን ዋናዋና ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን ምክር ቤቱ በዝርዝር ተመልክቷል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መኖራቸውን፤ እህት እና አጋር ፓርቲዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች በመልካም ጅምርነት የገመገመው ምክር ቤቱ በቅርቡ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ያለው እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ኢህአዴግ የቃል ኪዳን ሰነዱን አክብሮ በመንቀሳቀስ ሃላፊነቱን በተሟላ መልኩ እንዲወጣ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ህገ መንግስቱን፤ የሀገሪቱን ህጎች አክብረው በሰላማዊ የሀሳብ ትግል ብቻ በመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ውስጥ ያለባቸውን ሃላፊነት ተረድተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ከፖለቲካዊ ስራዎች አንፃር ሰፊ ውይይት ከተካሄደባቸው ጉዳዮች 
መካከል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት ይገኝበታል። ምክር ቤቱ በእህት ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል። ከዚህ አኳያ መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ፍጹም ነጻ በሆነ መንገድ ሀሳብ እንዲንሸራሸርና በመጨረሻም አገርንና ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡

በኢኮኖሚው መስክ የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ሀገራዊ የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን በማስተካከል ረገድ በጎ ሚና እንደነበራቸው የተመለከተው ምክር ቤቱ በተለይም ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል ትርጉም ያለው ስራ እንደተሰራ ገምግሟል። በዚህ መስክ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆኑም ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና ችግሮች በአግባቡ ያልተቀረፉ በመሆናቸው መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት መረባረብ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አስምሮበታል።

የወጣቶችን የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለይም የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች ያሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ፍላጎት አንጻር አሁንም ከለውጡ በሚገባው ደረጃ ያልተጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን ምክር ቤቱ በአጽንኦት ገምግሟል። በተጨማሪም ወጣቶቹ ያሏቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄዎች ገና በተሟላ ሁኔታ አለመመለሳቸውን አይቷል። በመሆኑም የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ በቀሪ የበጀት አመቱ ወራት ልዩ አገራዊ አጀንዳ እና የርብርብ ማዕከል እንዲሆን ምክር ቤቱ ወስኗል።

በየአካባቢው የሚታዩ ከመልካም አስተዳደርና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠንክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በአጽንኦት ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ በፀጥታና ፍትህ ስርዓቱ ላይ የተካሄደው ሪፎርምና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ በመቀልበስ ሀገራዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ የላቀ ሚና እንደነበራቸው በመገምገም የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ያሉ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውም ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል። ከዚህ አንፃር ማንኛውም ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልፅ ተለይተው በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸውና መንግስትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ሃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባው የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ አኳያ ክልሎች እና የየአካባቢው መዋቅር የየራሳቸውን ህገ መንግስታዊ ግዴታ እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ባለፉት ጊዚያት በአንዳንድ አካበቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ላይ በጥልቀት የተወያየው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመስለ አስፈላጊውን ጥረት እንዲደረግ አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡

ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነት መመስረቱና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እየተካሄደ መሆኑን የገመገመው ምክር ቤቱ በተለይ ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ሁለቱ ሀገራት ያሏቸውን ባህላዊ፣ የኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ዕድሎችን አሟጦ መጠቀም በሚያስችል መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለውጡ ሰፊና ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ክብርን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ የድርጅቱ ቀዳሚ ተልዕኮዎች መሆናቸውን አስቀምጧል። በመሆኑም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችንና ድሎችን የሚያሰፋና ጉድለቶችን የሚያርሙ እንቀስቃሴዎች በጊዜ የለንም መንፈስ መፈፀም እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ አውታሮች ግንባታ ላይ በጥልቀት የመከረው ምክር ቤቱ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በቀጣይ ጊዜ በተለይም ለመስኖ ልማት የሚሰጠውን ትኩረት እንደተጠበቀ ሆኖ በቀሪ ወራት በመኸር ስራ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማነቃቃት መረባረብ እንደሚገባም ዝርዝር አቅጣጫ አስቀምጧል።

የመገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ለውጡንና ትሩፋቶቹን እንዲሁም ያሉበትን ተግዳሮቶች በተመለከተ በስፋት መዘገባቸው ሀገራዊ አንድነት በማምጣት ረገድ አወንታዊ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ተመልክቷል። ሚዲያው ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ መሆኑም በአዎንታ የሚታይ ለውጥ ነው ብሏል ምክር ቤቱ። ሆኖም ከኋላው ታሪካችን ትምህርት በመውሰድ የወደፊት ተልዕኳችንን ለማሳካት የሚያግዙ መልዕክቶችን ከመቅረፅ ይልቅ ባለፉት ጉድለቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ብሶትን ማራገብ የሚታይበት በመሆኑ በቀጣይ መታረም እንደሚገባው አሳስቧል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ዴሞክራሲውን የማቀጨጭ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገምግሞ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል። የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነም ምክር ቤቱ አምኖበታል።

ምክር ቤቱ ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ በስፋት የተወያየ ሲሆን ለዉጡ አሁንም ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዳይጓዝ፤ ከተቻለም እንዲቀለበስ የሚጥሩ ሃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አይቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከጽንፈኛ ብሄርተኝነት፤ ስርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ፈተናዎች የአገራዊ አንድነታችንን ችግሮች በመሆናቸው በተባበረ ክንድ በመፍታት፤ ለውጡን ማስቀጠልና ማስፋት ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ አስተሳሰቦችን መግራትና ተግባራትን መግታት ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተልዕኮ መሆኑን አስምሮበታል።

በመጨረሻም የኢሕአዴግ ምክር ቤት በቀረበው ሰነድና ሪፖርት ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ስለሆነም የኢህአዴግ ምክር ቤት የድርጅቱ አመራር፣ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና መላው የሀገራችን ህዝቦች የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያስተላልፋል።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት
ሚያዚያ 9ቀን 2011 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *