የአጤ ቴዎድሮስ የልጅ ልጆች

አጤ ቴዎድሮስ “መይሳው ካሳ” እያሉ ይፎክሩ ነበር አሉ። ጠላታቸውን ጥለው ሲሸልሉ “መይሳው ካሳ፣ አንድ ለናቱ ሺ ለጠላቱ” ብለው ይፎክሩ እንደነበር ይነገራል።

ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት አጤ ቴዎድሮስ፣ ያለሙትን ለውጥ ለማምጣት ሳይሳካላቸው ከሀገር ውስጥና ውጪ በተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ ምክንያት የእንግሊዝ ጦርን ተፋልመው በሚያዚያ ወር 1860 መቅደላ አምባ ላይ እራሳቸውን ሰዉ።

በመቅደላ ጦርነት ወቅት ለእንግሊዞች እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸውን ያጠፉት የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላም ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው በቅርቡ ነው።

አጤ ቴዎድሮስ በጀግንነት እና በሀገር አንድነት ያልተነሱበት የኢትዮጵያ ጫፍ ያለ አይመስልም። ቴዎድሮስ “አጤ” ከመባላቸው በፊት ስማቸው ካሣ ኃይሉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ አጤ ቴዎድሮስ የተባሉት የሰሜኑን ገዥ ደጃዝማች ውቤን፤ ደረስጌ ላይ ድል አድርገው ዘውድ ከጫኑ በኋላ ነው።

• የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ሊመለስ ነው

• ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

አጤ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሥነ ጽሑፉ ዓለም ውስጥም ስማቸው ገናና ነው። በልቦለድ ሥራዎች ውስጥ እንፈልጋቸው ብንል የብርሃኑ ዘሪሁን የቴዎድሮስ እንባ፣ የአቤ ጉበኛ አንድ ለናቱን እናገኛለን፣ በተውኔት ደግሞ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን አጤ ቴዎድሮስና የጌትነት እንየው የቴዎድሮስ ራዕይን መጥቀስ እንችላለን።

ስማቸው በዘፈን ያልተነሳበት፣ ያልተወሳበትም ዘመን የለም። ኢትዮጵያን ያነሳ፣ ጎንደርን የጠቀሰ ስለ አጤው ያዜማል።

ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር፤

ለአንት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሚለው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የቅርብ ጊዜ ዜማን ማስታወስ በቂ ነው።

አጤ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከእንግሊዝ አገር ከመጡ 32 ሺህ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ተከትሎ በሀገሪቷ ላይ ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈፀመ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

የእንግሊዝ ወታደሮች የዘረፉት መጻሕፍትን፣ የተለያዩ ከወርቅ የተሠሩ ቅርሶችን፣ መንፈሳዊ ሥዕሎችን፣ ታቦታትን፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን ልጃቸው አለማየሁ ቴዎድሮስንም ጭምር ነው።

አለማየሁ በሰው ሀገር በብቸኝነት፣ በለጋ እድሜው መሞቱና እዚያው መቀበሩ ይታወቃል። ሌሎች የአጤው ዘመዶችስ? የት ናቸው?

የአጤ ቴዎድሮስ የልጅ ልጆች

ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን የአጤ ቴዎድሮስ ልጅ ተብሎ የሚታወቀው ልዑል አለማየሁ ብቻ ነው። በርግጥ አጤው ሌላ ልጅ የላቸውም? ስንል እንፍራንዝ ያገኘናቸውን ወ/ሮ አበበች ካሳን ጠየቅናቸው።

በእርግጥ በጊዜው በአጠገባቸው የተገኘው ልጅ እርሱ ነበር። ለዚህም ይሆናል የእርሱ ስም ብቻ የሚነሳው ሲሉ ሌሎች ስድስት ልጆች እንዳሏቸው ነገሩን። እኛም እስቲ ስማቸውን ይዘርዝሯቸው ስንል ጠየቅን፦

“በጎጃም ኃይሉ ቴዎድሮስ፣ በወሎ ይማም ቴዎድሮስ፣ በትግራይ አልጣሽ ቴዎድሮስ፣ በጎንደር አለማየሁ ቴዎድሮስና መሸሻ ቴዎድሮስ” ሲሉ ዘረዘሯቸው።

ታዲያ እርስዎ አጤ ቴዎድሮስን ይዛመዳሉ ማለት ነው? ቀጣይ ጥያቄያችን ነበር።

“ዛዲያሳ” የእርሳቸው መልስ።

የማን ልጅ ነዎት ተከታይ ጥቄያችን አደረግን

የደጃዝማች ካሳ መሸሻ ቴዎድሮስ፣ የአጤ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ልጅ፣ የልጅ ልጅ ነኝ፤ ብለውናል።

ከእንፍራንዝ ወጥተን ጎንደር ስንሄድ ያገኘናቸው የአጤ ቴዎድሮስ አራተኛ ትውልድ ደግሞ ስለ ቤተሰቦቻቸው ሲያስረዱ፤ አጤ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ልጃቸውን ራስ መሸሻን ወለዱ፣ ራስ መሸሻ ቴዎድሮስ ደጃዝማች ካሳን፣ ደጃዝማች ካሳ ባንች አምላክ ካሳን ወለዱ ከዚያም እኔ ፋሲል ሚናስ ተወለድኩ ይላሉ።

 እምቦጭ የጣና ቂርቆስ መነኮሳትን ከገዳሙ እያስለቀቀ ነው

ሌላው እዚያው ጎንደር የሚኖሩት የአጤው ቤተሰብ አለማየሁ ቴዎድሮስ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አጤ ቴዎድሮስ መሸሻ ቴዎድሮስ፣ መሸሻ ቴዎድሮስ ደግሞ ደጃዝማች ካሳን፣ ደጃዝማች ካሳን ደግሞ እናታቸውን ሙሉ ካሳን መውለዳቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ የንጉሱ አራተኛ ትውልዶች የአጤውን ታሪክ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን እንደ ራሳቸው ቤተሰብ ታሪክ እየሰሙ ነው ያደጉት።

ነዋሪነታቸው እንፍራንዝ የሆነው ወ/ሮ አበበች ስለ አጤ ቴዎድሮስ ደግነት፣ ሩህሩህነት፣ ጀግንነታቸውን እየሰሙ ነው ያደጉት። “ለወስላቶች አይቀጡ ቅጣት የሚቀጡ ለሀገራቸው ደግሞ ባለ ራዕይ የነበሩ መሆናቸውን እየሰማሁ ነው ያደግኩት።”

እንደውም እቴጌ ተዋበች ከሞቱ በኋላ ሆድ እየባሳቸው ሄደ እንጂ ከዚያ በፊት ሐይማኖተኛና ጥሩ ሰው ነበሩ ይላሉ ወ/ሮ አበበች።

የአጤው ቅርስ ይኖርዎት ይሆን ቀጣይ ጥያቄያችን ነበር?

ንግሥት ቪክቶሪያ የሰጠቻቸው ደወል አለኝ። ሌላው ግን ይላሉ ወ/ሮዋ በደርግ ዘመን መትረየስ አለሽ እያሉ ሲያንገላቱኝ፣ ሲያስሩኝ ቀበርነው። ስፍራውን አሁን ሰዎች ቤት ሰርተውበታል። ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብሎ የተፃፈበት ጎራዴ ሁሉ ነበር ይላሉ። ከጎራዴው ጋር ሌሎች ትናንሽ ቅርሳ ቅርሶችንም ቀብረናል ሲሉም ያስታውሳሉ።

እነ ፋሲል እና አለማየሁ ጋር ግን የአጤ ቴዎድሮስ ማስታወሻ የሚሆን ምንም ነገር በቤታቸው የለም።

በስማቸው ፎክረው ያውቁይሆን?

አለማየሁ ቴዎድሮስና ፋሲል ሚናስ በስማቸው ብቻ በመኩራት በባዶ መኖር አትችልም ይላሉ። የአጤ ቴዎድሮስን ስም ለመጥራት እና የልጅ ልጅ ነኝ ለማለት የራስህን ሥራ ሥራ እየተባልን ነው ያደግነው ሲሉም ያስረዳሉ።

አቶ ፋሲል አክለውም ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያደረጉትን ነገር በታሪክም በታላላቆቻቸውም ሲነገራቸው ማደጋቸውን ያስታውሳሉ።

ወ/ሮ አበበች ከጎንደር ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከእንግሊዝ ድረስ እየመጡ ቴዎድሮስን ያሉ፣ ስለ እርሱ ለማወቅ የሚፈልጉ እንደሚጠይቋቸው ይናገራሉ። እንደው ፎክሪ ፎክሪ ካላቸውም ‘የቴዎድሮስ ዘር’ ሲሉ ይፎክራሉ።

የአጤ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ተመለሰ ሲሏቸው የተሰማቸውን ደስታም ሲገልጡም “የልዑል አለማየሁ አፅም ቢመጣ” ይላሉ። ከዚያ በኋላ የሄደው ቅርስ ሁሉ ቢመለስ ደስ ይለኛል ብለዋል።

አለማየሁና ፋሲልም የአጤው ቁንዳላ መመለሱ የፈጠረባቸውን ሲናገሩ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ነገር መሆኑን በመጥቀስ የተሰማቸውን ደስታ ነግረውናል። ቴዎድሮስ አለማየሁ አክሎም “ስሜን እንደ እርሳቸው የሚያስጠራ ታሪክ መሥራት እፈልጋለሁ” ይላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *