ጋዜጣዊ መግለጫ ከአማራ ክልል ቃል አቀባይ።

⬆️
የጋዜጣዊ መግለጫው ዝርዝር ⬇️

የአማራ ክልል ቃል- አቀባይ አቶ አሰማኸኝ አስረስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጃዊ ወረዳ ላይ ደረሰ ስለተባለው ግጭት እና ሞትን አስመልክቶ ዛሬ ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተወሰደ:

  • ሚያዝያ 17 ግጭቱ ከጀመረ በሁዋላ እና በቀጠሉት ቀናት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በዚህ ቀን በሁለት ግለሰቦች መሀል በተፈጠረ አለመግባባት የአንድ ጉሙዝ ህይወት አልፏል። ከዛ ቀጥሎ በብቀላ መልክ በአካባቢው በነበረው የአማራ ማህበረሰብ ላይ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ግድያዎች ተፈፅመዋል።
  • ግድያዎቹ አሁን ላይ የሰው ልጅ በደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ እንዲሁም የሰውን ልጅ አጠቃላይ ክብር እና የደረሰበትን ልእልና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ ለኢትዮጵያውያን የማይመጥን በጫካ አስተሳሰብ የተመራ እና በጨካኝነት የተተገበረ ግድያ ነው።
  • በቤንሻንጉል የተፈፀመውን ድርጊት ተከትሎ፣ በዛ ምክንያት የተቆጡ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ወይም በሌላ ምክንያት ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ሀይሎች በአማራ ክልል የአዊ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ግጭት አስነስተው እዛም የሰው ህይወት አልፏል። ይህ የሆነው በተለይ ሚያዝያ 21 ቀን ነው። ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ቡድን ወደ ስፍራው ተልኮ እያጣራ ነው ያለው።
  • በጃዊውም ሄነ በቤንሻንጉል የተከሰተው በፍፁም ተቀባይነት የሌለው እና ሊወገዝ የሚገባ ነው። ጥፋትን በጥፋት የመመለስ አጀንዳ ሌላ ጥፋት እያስከተለ ይሄዳል እንጂ ጉዳዩን መፍትሄ አይሰጠውም።
  • በዚህ ዙርያ ሰሞኑን የሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች አሉ። አንዳንድ የሚድያን ስም የያዙ ግን የአንድን ግለሰብ ወይም ፓርቲ ልሳን የሆኑ ኔትዎርኮች በጉዳዩ ላይ ማህበረሰቡ የተንሸዋረረ ምልከታ እንዲኖረውና ግጭቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ግጭቱን በሀሰተኛ ምስል እና ትርክት በማቅረብ ውዥንብር ለመፍጠር እየሞከሩ ናቸው።
  • በፖለቲካ ትግል አጣነው ብለው የሚያስቡትን ሁሉ የሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህብረተሰቡን ውዥንብር በመክተት እኛ ካልሰራነው የሚል አቋም ይዘው የሚንቀሳቀሱ አሉ። አንዳንዶቹ የአማራው መደራጀት እና መጠንከር የማይዋጥላቸው አማራ ጠል ሀይሎችም አሉ።
  • አንዳንዶቹ ጉዳዩን የሚገልፁት ግለሰቦች (ወይ በሚድያዎቻቸው) የተለያየ መንገድ አላቸው። አማራ ጠል ትርክታቸውን ወደፊት እንዲያስኬድላቸው የሚፈልጉ አካላት (በዚህ ጥቃት ዙርያ) የሚገልፁዋቸው ቁጥሮች አሉ። ያ ተቀባይነት የለውም። ያልተረጋገጠ መረጃ ነው። መረጃ ትክክል የሚሆነው ከትክክለኛው ምንጭ ሲገኝ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *