የአማራ ክልል ዓመታዊ የአትሌቲክስ ክለቦች ውድድር ተጀምሯል።

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 9/2011ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የ2011 ዓመታዊ የአትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በባሕር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

እርምጃ፣ ሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ የስፖርት ዓይነቶችን ባካተተዉ ውድድር በአማራ ክልል የሚገኙ 11 ክለቦች እና ሁለት ማሰልጠኛ ማዕከላት እየተሳተፉ ነው፡፡ አዊ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ዳባት፣ ዋልያ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ አብቁተ፣ አማራ ማረሚያ፣ ጥረት ኮርፖሬት፣ አውስኮድ፣ ጭልጋ እና አማራ ፖሊስ በክለብ ደረጃ እንዲሁም ደብረ ብርሃን እና ተንታ በማሰልጠኛ ማዕከላት ደረጃ ነው እየተሳተፉ ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዱኛ ይግዛው በውድድሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ዓላማዉ በ48ኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አማራ ክልልን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመል ነው ብለዋል፡፡ በክለቦች ታቅፈው ዓመቱን ሙሉ ውድድሮችን ሲያካሂዱ የነበሩ አትሌቶችን አቅም መፈተሽም ሌላው ዓላማ ነው።

በዛሬው መርሃ ግብር የወንዶች 10ሺህ ሜትር እና የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ፣ ስሉስ ዝላይ፣ የሴቶች ዲስከስ ውርወራ፣ የወንዶች ርዝመት ዝላይ እና ዲስከስ ውርወራ ውድድሮች ይደረጋሉ።
በሁለቱም ጾታዎች ከ4 መቶ እስከ 8 መቶ ሜትር የማጣሪያ የሩጫ ውድድሮችም ይካሄዳሉ።

ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 13/2011 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ 48ኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 4/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ዓመት ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር የአማራ ክልል አራተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *