#የዴርቶጋዳ_ተከታታይ ክፍል በአንድ ጥራዝ ለገበያ ውሏል!

የሆነው ሆነና እንኳን ደስ አለህ፡፡ መፅሐፍን አምጦ ከመውለድ ይልቅ የህትመትን አቀበት አልፎ ለአንባቢያን ማድረስ ፈታኝ እንደሆነ ትንሽ ታዝቢያለሁ፡፡ የደራሲ ትርፉ ጭንቀት፥ ጭቅጭቅና ትችት እንደሆነም እንዲሁ፡፡ በአማካኝ ከ75-90% የሚሆነው የመፅሐፉ ዋጋ የደራሲውን ደጅ ሳይረግጥ መንገድ ላይ ተንሸራቶ የሚቀር ነው፡፡ እኔ እጄን ሰብስቢያለሁ፡፡ ለወረቀትና ለህትመት ውድነት (ለእውቀት ብርሃን) ግድ በሌላት ሀገር፥ ነገ ለማሳተም ያሰባችሁ ፅናቱን አብሮ ይስጣችሁ፡፡ አታሚዎችም እንዲሁ፡፡ ደራሲ ይስማዕከ በጣም እልኸኛ ነው፡፡ በእልኸኝነቱና በጥንካሬው፣ የደረሰበት አደጋና እንደ ህፃን በየቀኑ የሚንከባከበው ህመሙ ሳይበግረው፥ አሉቧልታና የጭን ቁስል የሆኑ ውስጣዊ ጉዳዮች ተስፋውን ሳያጨልሙት፥ #የዴርቶጋዳን ተከታታይ ክፍል በአንድ ጥራዝ አዘጋጅቶ እነሆ ብሏል፡፡

ይስማዕከ አንድ አባባል አለው “አንተ ስለራስህ ካልተናገርህ፥ ስለራስህ ያለውን ክፍተት ሌሎች በአሉቧልታ ይሞሉታል” ይላል፡፡ “ተራኪው” የራሱ የሚተረክ ታሪክ እንዳለው ግን ቃሉን ሳይሆን “መረጃዎችን” ዋቢ አድርጎ ሌላ ተራኪ አንድ ቀን ይፅፈዋል፡፡ ከመመርመር ማዬት፥ ከማዬት-መስማት፥ ከመስማት-መናገር የሚቀናን ህዝቦች ስለሆንን ብዙ ማለቱ ጥቅም የለውም እንጂ ዴርቶጋዳን ለመፃፍ የሄደበት ርቀት ሌላ አንድ ጥራዝ ሆኖ በአንክሮ ይነበብ ነበር፡፡ በባለጊዜዎች መረብ ወስጥ ሆኖ፣ ዛቻና ግርፋቱን ችሎ ለመፃፍ ያደረገውን ትግል ከተራኪው አፍ ሲወጣ አልሰማንም፡፡ “የራሱን ቁስል በጉያ፣ የህዝብን ገድል በገበያ” የሚተርክ እንበለ ከንቱ ያልሆነ ሰው ብዙ አልታደልንም፡፡ በነጠላ የፌስቡክ ፅሁፍ አካኪ ዘራፍ ብሎ “ስለ ፅድቁ የሚተነትን” አፈ ቀላጤ በበዛበት ዘመን የመሰል የእሳት እራት ፀሐፊዎችን ድካም አደባባይ ላይ ማስጣት ዋጋውን የምሸት ገበያ ማድረግ ነው፡፡

ዴርቶጋዳ በአንድ ጥራዝ መዘጋጀቱ ለጊዜው ኪስ የሚዳብስ ቢመስልም ጥቅሙ ግን ብዙ ነው፡፡ ያም ሆኖ 5 መፅሐፍ በ500 ብር አበርክቷል፡፡ ልጆቻችን እንዲነቃቁና በመፅሐፉ የተጠቀሱ ሚስጥራዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ በዚያውም የጠፋችዋን ኢትዮጵያ እንዲፈልጉ ይረዳል፡፡ ይስማዕከ የተረገዙ ሁለት ሶስት አዲስ ነገሮች እንዳሉት ባውቅም፥ በርትቶ ለአንባቢያን እንዲያደርስ በሞራል መደገፍ ጥቅሙ ለእሱ ሳይሆን ለአንባቢያን ነው፡፡ የገንዘቡ ጉዳይ ከላይ እንዳነሳሁት ነው፡፡ ትርፉ ጨጓራና መከራ ነው፡፡ ስፖንሰሮችም ለመፅሐፍ ሲሆን ዳገት ይሆንባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የእኛ ሀገር ሀብት በእውቀት የመጣ አለመሆኑ ይመስለኛል፡፡ በእውቀትና በጥበብ የማይመራ ህዝብ ደግሞ ፍፃሜው ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

ለደራሲው አንድ ትልቅ አሳይመንት ሰጥቸዋለሁ-ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም አሻራ፡፡ ጊዜው ሲደርስ እናየዋለን፡፡ እስከዚያው ግን አግዙት፡፡ መፅሐፉን ያላነበባችሁ እንድታነቡት፥ ያነበባችሁ ደግሞ ሸልፋችሁ ላይ አስቀምጣችሁ ጊዜ ስታገኙ አንዳንድ ሀሳቦች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር እንድታደርጉ በአክብሮት እጠቁማለሁ፡፡ አሁንም የዚች ሀገር ተስፋና ስልጣኔ ያለው ማህፀኗ ውስጥ ነው፡፡ ማህፀኗ ውስጥ ታሪክ፥ እውነት እና እውቀት አለ፡፡ ማህፀኗን ፈልጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *