ኦሮምያ 70.1 ቢልዮን፣ አዲስ አበባ 48.7 ቢሊዮን፣ አማራ 47.4 ቢሊዮን ብር – የ2012 ዓም በጀት!

የ2012 ዓም የክልሎች በጀት!! ኦሮምያ 70.1 ቢልዮን፣ አዲስ አበባ 48.7 ቢሊዮን፣ አማራ 47.4 ቢሊዮን ብር

(Habtamu Ayalew)

የበጀት ድልድሉ የዛሬ ብቻ አይምሰልህ ያደረ ስካር ነው !!
————————————————
“የተሳከረውን የበጀት ድልድል በተመለከተ ስካሩ ያደረ ነው ።

ወደ ዓመታዊ በጀቱ ከመዝለቄ በፊት በ2009ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ከተለቀቀው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ኦሮሚያ 6.2 ቢሊዮን ብር እንደወሰደ :: የአማራ ድርሻ ደግሞ 2. 4 ቢሊዮን እንደነበር በማስታወስ ስካሩ የዛሬ ሳይሆን ያደረ እንደነበር ይመዝገብልኝ ።
አሁን ደግሞ ሌላኛውን ያደረ ስካር ተመልከቱት :-

ኦሮሚያ
በ2010 የበጀት ዓመት 55.8 ቢ
በ2011 የበጀት ዓመት 63.4 ቢ
በ2012 የበጀት ዓመት 70.1 ቢ

አማራ
በ2010 የበጀት ዓመት 37.6 ቢ
በ2011 የበጀት ዓመት 43.5 ቢ
በ2012 የበጀት ዓመት 47.4 ቢ

(ምንጭ:-የገንዘብ ሚኒስቴር የሦስት ዓመታት ተናጠላዊ ሪፖርቶች)

ይሄ የጎንዮሽ ያለመመጣጠን (Horizontal imbalance) አገሪቱ ገቢር እያደረገች ስላለችው “የፊስካል ፌዴራሊዝም ” ደግመን ደጋግመን እንድንጠይቅ ያደርገናል።

ሌላው ጉዳይ ይሄ ፊስካል ፌዴራሊዝም ማዕከላዊውን አገዛዝ በገቢ ምንጭ በማሳበጥ በአንፃሩ ክልሎች አነስተኛ ታክስ እንዲሰበስቡ በማድረግ ገድቦ የመያዝ ባህሪ አለው ። ሪፖርቶችን ብትመለከቱ አስደንጋጭ የሆኑ አህዛዊ መረጃዎችን ታገኛላችሁ ። አንዳንድ ክልሎች (ታዳጊዎቹ) ከ90-92% የበጀት ድጎማ ከፌዴራሉ መንግስት ያገኛሉ ። ክልላዊ አቅማቸው ከ8-10% ድረስ ብቻ ሆኖ ይታያል ።

አማራ “ክልል” ታክስ የመሰብሰብ አቅሙ 12 ቢሊዮን አይደርስም ። በአማካይ 76% የሚሆነውን የክልሉን በጀት የሚሸፍነው ከፌዴራል መንግሥቱ እየተንጠባጠበ በሚለቀቅ የድጎማ በጀት ነው ።

ከታክስ አሰባሰብ አኳያ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎቹ ላይ እጁን አስረዝሞ አቅሙን በገቢ ያፈረጠመበት ሁኔታ መኖሩን ያጤኗል ። ለሁሉም ዶ/ር አቡ የተባሉ አጥኝ “Fiscal federalism and its discontents: Theory and Policy” በሚለው የጥናት ውጤታቸው በክልሎች መካከል ያለውን ያለመመጣጠን ለማርገብ አንዱ አማራጭ ክልሎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሊበደሩ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይገባል ሲሉ ምክረ-ሐሳባቸውን አቅርበዋል ። ለጊዜው የሰውየውን ምክረ-ሐሳብ ገቢር ለማድረግ የሕግ ማሻሻያ ግድ ይለናል ። አለያማ ከአስራ አምስት በላይ ዞኖች ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ 174 ወረዳዎች ላሉት አማራ ክልል ይህችን ታህል ዓመታዊ በጀት ከመደበኛ በጀት ተሻግራ በምን አግባብ የካፒታል ፍላጎትን የሚያሟላ በጀት ሊሆን ይችላል?

በነገራችን ላይ ከስድስት ወር በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት አማራ ክልል ላይ ሥራ አጥነቱ 28% መድረሱን ገልፆል ። ይሄ እነሱ ያመኑት ነው ። እውነተኛውን የሥራ አጥነት ቁጥር ሪፖርቱ ላይ የተመለከተውን አሃዝ በእጥፍ ብትመቱት ከእውነታው ብዙ አትርቁም ። በተለይ በገጠር ያለው ስራ አጥነት ከግምት በላይ ነው ። የመንግሥት ስራ ፈጣሪነት ሚና በዚህ ውስን በጀት የት ድረስ ሊሆን ይችላል?

85% ከመቶ የሚሆነው ወገናችን በገጠር ነው የሚኖረው ። ሜትሮ ፖሊታንት የሆኑ ከተሞችን መገንባት ህልም ሆኗልና ገጠሩን እናስበው!

ለቀጣይ ዓመት ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች እጅግ በጥቂቱ:-
——————————————————————–
1. የመስኖ ልማታችን የት ላይ ነው?
2. የገጠር መንገድ ስራውስ?
3. የተዘነጋው የማህበራዊ ዘርፍ መሠረተ ልማትስ የት ላይ ነው? (ለቀጣይ ዓመትም ት/ት በዳስ? ለወሊድ በቃሬዛ የምትሄድ እናት? )
4. ትዝ ብሎን የማያውቀው የቅድመ-መደበኛ ትምህርት እና የጎልማሶች ትምህርትስ ታሳቢ ነውን?
5. በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋም (FTC) ግንባታ ታስቦበታል?
6. የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦቱ ጉዳይ? …
ወዘተ ጉዳዮች እንቅልፍ ሊነሱን የሚገቡ የልማት አጀንዳዎች ናቸው ። የራስ አቅምን አሟጦ መጠቀም ይገባል ። ከራስ አቅም አልፎ ክልሉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆን ማድረግ ግድ ይላል ።

በተረፈ ይሄን የበከተ ፊስካል ፌዴራሊዝም መልክ እንዲይዝ ለማድረግ አቅሙ ያላቸው ምሁራን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን ሊያቀርቡ ይገባል ። ያኔ-ካደረው ስካር የተላቀቀ ፖሊሲ ገቢር ማድረግ እንችል ይሆናል ።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *