ማዕድኑ በህገወጥ አሰራር ተጠልፏል

በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ፣ ለጌጣጌጥ፣ ለኮንስትራክሽን፣… ስራዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ማዕድናት ይገኛሉ:: ለአብነት ሲሊካ ሳንድ፣ ጅፕሰም፣ ብረት፣ ኦፓል፣ ወርቅ እና ሌሎችም እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ:: ከነዚህ ማዕድናት መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጌጣጌጥና ለመዋቢያ ስራ በመዋል የአለምን ገበያ እየተቆጣጠረ ያለው ኦፓል በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በስፋት ይገኛል::

በደቡብ ወሎ ዞን በደላንታ ወረዳ ከሚገኙ 31 የገጠር ቀበሌዎች መካከል 27ቱ ቀበሌዎች በኦፓል ማዕድን የበለፀጉ ናቸው:: ይህን የከበረ ማዕድን ህግና መመሪያ አዘጋጅቶ በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ ህገ ወጦች እንዲከብሩበት አለፍ ሲልም ለአካባቢው የፀጥታ ስጋት መንስኤ እንዲሆን በር ከፍቷል::አቶ በላይ አድማሱ በደላንታ ወረዳ የወገል ጤና ከተማ ኗሪ ናቸው:: እሳቸውም እንደሚሉት ኦፓል በአካባቢው መኖሩ ጥቂት ስዎችን ከመለወጥ ውጪ ለወረዳውም፣ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለሀገር ያበረከተው ፋይዳ የለም:: 
አቶ በላይ ይህንን በኦፓል ማዕድን ላይ ያንዣበበውን ህገ ወጥነት ሲያብራሩም በወረዳው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ህገወጥ የኦፓል አምራቾች አሉ:: በአንድ ወቅት በወገል ጤና ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ የአካባቢው ማህበረሰብ አንድ ኪሎ ኦፓል ሳያወጡ 18 ኩንታል ኦፓል እንደተሸጠ ተደርጐ ሀሰተኛ ደሰረኝ መቆረጡን በቅሬታ መንገድ በስፋት ሲነሳ እንደነበር አቶ በላይ ያስታውሳሉ:: በዚህ ህገወጥ ተግባር ከማዕድን የሚገኘው ስድስት በመቶ የሀገር ውስጥ ገቢ /ሮያሊቲ/ በአግባቡ ስላማይገባ በወረዳው እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው::

የህገ ወጥነት መንሰኤ

ከኦፓል ምርት ጋር በተያያዘ በወረዳው ህገወጥነት ተስፋፍቷል:: ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ፣ ከፀጥታና ከሠላም መደፍረስ ጋር የሚነሱ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን እና የጋራ ሀብትን በህጋዊ መንገድ በጋራ ከመጠቀም አኳያ የሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች በየጊዜው እየተበራከቱ የመጡት ከማዕድን ሀብቱ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አቶ በላይ አስረድተዋል:: ˝ይህ የእኔ ቀበሌ ነው? ማዕድን ፍለጋ ሌላው ድርሽ ማለት የለበትም ̋ የሚል የስገብግብ አስተሳሰብ በወጣቶች ዘንድ መበራከትም ሌላው ለወረዳው የፀጥታና የሰላም መደፍረስ አይነተኛ ምክንያት ሆኗል::

አቶ ተስፋዬ አጋዥ በደላንታ ወረዳ ኗሪ ሲሆኑ ኦፓል አምራች ነጋዴ ናቸው:: “በኦፓል ማዕድን የአካባቢው አምራችም ሆነ አዘዋዋሪ እየተጠቀመ አይደለም:: ህገ ወጥ ደላሎችና ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሀብቶች እየበሉን ነው::” በማለት ይናገራሉ:: “ለምሳሌ እኔ 520 ሺህ ብር የኦፓል ማዕድን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሸጨ ያለ አግባብ 52 ሺህ ብር ክፈል ተብዬ ተገድጄ ነበር፣ በስንት ትንቅንቅና ትግል ነው ትክክለኛውን ስድስት በመቶ ከፍዬ መሸጥ የቻልኩት” በማለት በአምራቾች ላይ የሚደርሰውን ህገ ወጥ አሰራር ይናገራሉ::

“አዲስ አበባ ላይ ህገ ወጥ ደላላ በዝቷል ሁለት በሁለት በሆነች ኮንቴይነር ውስጥ ተቀምጠውና የኦፓል ማዕድን ላኪ የሚል ታፔላ ለጥፈው አይን ያወጣ ህገ ወጥ ድርጊት ሲፈፀሙ እየተመለከተ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴሩም ሆነ የክልሉ ማዕድን ቢሮ ጣልቃ ገብቶ የማስተካከል ስራ ሲሰራ አይታይም:: ይህም ችግሩ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ተያያዥነት ያለው መሆኑን ያመላክታል” ሲሉ ይገልፃሉ:: ከላይ ጀምሮ ህገ ወጥነት የሚታይበት አሰራር እንዳለውም ተናግረዋል::

አቶ በላይ የተስፋዬን ሀሣብ በመጋራት በህገ ወጥ ደላላዎችና የኦፓል ላኪዎች አማካኝነት በርካታ የደላንታ ኦፓል አምራቾች ሀብታቸውን እንደተጭበረበሩ ይገልፃሉ:: ለምሳሌ ይላሉ አቶ በላይ አንድ ህንዳዊ የኦፓል ላኪ ፈቃደ ደሳለኝ ከተባለው የደላንታ ኦፓል አምራች 11 ሚሊዮን ብር እና ከሌሎችም አምራቾች መጠኑ የተለያየ ገንዘብ ይዞባቸው እንደተሰወረ ድፍን የደላንታ ነዋሪ የሚያውቀው ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ:: ይህም የሆነው ህጋዊ አሰራር ስላልተዘረጋለት በመተማመን ላይ ብቻ የተመሠረተ አሰራርን ስለሚከተሉ የተፈጠረ መሆኑንም ይገልፃሉ::

በኦፓል ምርት የደላንታ ወረዳ አምራችም ሆነ አዘዋዋሪው በአግባቡ አልተጠቀሙበትም፤ በተቃራኒው ይበልጥ ተጠቃሚ የሆኑት ህገ ወጥ ደላላዎችና የውጭ ላኪዎች ናቸው:: ለዚህም ዋናው ምክንያት ኦፓል ማዕድን የማምረትና የመሸጥ ደምብና መመሪያ ተዘጋጅቶለት በህጋዊ መንገድ ማስተዳደር ስላልተቻለ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

የችግሩ ምንጭ

የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ጌታቸው የማዕድን ሀብቱ ከመጀመሪያ ጀምሮ ህጋዊ የሆነ አደረጃጀትና አሰራር ስላልተዘጋጀለት በወረዳው የሚገኙ 27 የኦፓል አምራች ማህበራት ህጋዊ መሠረት ኑሯቸው ትክክለኛ መስመሩን ተከትለው ብቻ እየሰሩ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ያስረዳሉ:: በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የማዕድን ብክነት መኖሩን ይገልፃሉ::

ወረዳው ዝናብ በሚጠፋበት ወቅት ለችግር የሚጋለጥ አካባቢ በመሆኑ ይህንን የኦፓል ማዕድን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዞ በዘመናዊ አሰራር በአግባቡ እና የህብረተሰቡን ህይወት በሚቀይር መልኩ ባለመቃኘቱ ህብረተሰቡን ከተለያዩ ችግሮች ሊታደገው እንዳልቻለም አቶ አርጋው ተናግረዋል::

የፌዴራል ማዕድንና ኢነርጅ ሚኒስቴር፣ የክልሉ ማዕድን ልማትና ማስፋፊያ ኤጀንሲ በተዋረድም ዞኑ እና ወረዳው ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት አይደለም:: በዚህም በወረዳው ህገ ወጥነት እንዲበራከት እና ኦፓሉም እንዲባክን ሆኗል፤ እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ:: ̋ሀብቱን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላችን ትልቅ ችግር ሆኖብን እያለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ ይህ ማዕድን አሁን ላይ ለአካባቢያችን ሰላምና ደህንነት ትልቅ የስጋት ምንጭ ሆኗል::” ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው ያክላሉ::

የኦፓል ማዕድን በሌለባቸው ቀበሌዎች የሚኖሩ ስራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተውና ማህበር መስርተው ማዕድኑ ባለበት አካባቢ እናመርታለን ሲሉ ̋ከእኛ አካባቢ ማንም አይገባም˝ በሚል እሰጥ አገባ በሚፈጠሩ ግጭቶች የወረዳው ሠላምና ፀጥታ አደጋ ላይ ሲወድቅ እንደነበር ነው የሚያስታውሱት::
ዋና አስተዳዳሪው ይህንን የፀጥታ ችግር ለመፍታትም ወረዳው የሀይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን በማስተባበር ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል::

የተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች “እኛ ዳቦ የምንቆርስበት የለንም፤ እናንተ እስከ አሁን ሀብትና ጥሪት አፍርታችኋል:: የማዕድን አስተዳደር መመሪያውም ሁሉም ዜጋ መጠቀም እንደሚችል ይገልፃልና ልንጠቀም ይገባናል” የሚሉ ወጣቶች በአንድ በኩል “በእኛ ቀበሌ ከእኛ ውጭ ማንም መግባትና መስራት አይችልም” የሚሉ ወገኖች በሌላ ጐራ ሆነው በወረዳው ሁለት ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎችም ተካሂደዋል:: በዚህም ምክንያት የአካባቢው ሰላም ስጋት ውስጥ ወድቋል:: ወረዳውም ሁኔታው ከአቅሙ በላይ እየሆነ መምጣቱንና በተደጋጋሚ ለፌዴራል ማዕድን ሚኒስትር ለክልል ቢሮም አሳውቋል:: ተገቢ የሆነ መፍትሄና ምላሽ ግን እያገኙ አይደለም፤ እንደ ዋና አስተዳዳሪው አስተያየት::

”የክልሉ ማዕድን ልማትና ማስፋፊያ ኤጀንሲም ሆነ ሌሎች የችግሩን አሳሳቢነት በጥልቀት ተረድተው ሊያግዙን አልቻሉም:: መመሪያው ገና አልተሟላም በሚል ምክንያት ለጉዳዩ መፍትሄ መስጠት አልቻሉም:: ጉዳዩ ግን ስር እየሰደደ እስከ ህይወት መጠፋፋት እየተደረሰ ነው:: እኛም ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ እየሆነብን መጥቷል” በማለት ዋና አስተዳዳሪው የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል::
“ሀብቱ ለሁለም በቂ ነው የፌዴራል ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርም ሆነ የክልሉ ማዕድን ልማትና ማስፋፊያ ኤጀንሲ በጋራ ሆነው የተደራጀ የአጠቃቀም ደምብና መመሪያ ተዘጋጅቶለት በአግባቡ አለመመራቱ ነው ችግሩ እየተባባሰ እንዲሄድ ያደረገው” ሲሉም አቶ አርጋው ያስረዳሉ::

መፍትሄው

በዘርፉ የሚታየውን ህገ ወጥ አሰራር ለመከላከል በደላንታ ወረዳ ኦፓልን ከዚሁ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል አሰራርን ለመዘርጋት ቋሚ የኦፓል የግብይት ማዕከል ለመገንባት ክልሉ ቦታ ተቀብሏል፤ የአፈር ናሙና ወስደዋል፤ ግንባታውንም በሦስት ወር ውስጥ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ተገብቶ እስከ አሁን ግንባታው እንዳልተጀመረ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል::
የአብክመ የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ለገሰ የኦፓል ማዕድኑ ከመጀመሪያም የክምችት መጠኑ ተጠንቶና ታውቆ መንግስትም እውቅና ኖሮት በህግና መመሪያ ተቃኝቶ አይደለም ማውጣት የተጀመረው:: በዚሀም ምክንያት የተደራጀ አሰራርን ባለመከተሉ ለህገ ወጥ ተግባር የተመቸ አድርጎታል በማለት ተናግረዋል::

ማንኛውም ማዕድን በህግና መመሪያ እንደሚተዳደር የሚገልፁት ዋና ዳይሬክተሩ በክልል ደረጃም የከበሩ ማዕድናት የሚተዳደርበት 678/2002 እና ሌሎች መመሪያዎች አሉ፤ እነዚህን መመሪያዎች በአግባቡ በመጠቀም ማዕድናቱን ማስተዳደር እንደሚገባም ጠቁመዋል::

አምራቹን ወጣት ተጠቃሚ አለማድረግ፣ በግብይቱ ላይ ህገ ወጥነት መበራከት እና የአመራረት ስርዓቱ ያልዘመነ መሆን ዋና ችግሮች መሆናቸውን በመግለፅ ህገ ወጥነቱን ለመከላከል ሁሉም አካል ከህብረተሰቡና ከወጣቱ ጋር በመሆን ርብርብ ማዳረግ እንደሚገባ ገልፀዋል::

ከአመራረት እስከ ገበያ ድረስ ያለውን ሁኔታ ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግም ከአዲስ አበባ እና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እስካሁን ድረስ የማናውቀውን የኦፓሉ የክምችት መጠን ምን ያህል እንደሆነና ለምን ያህል አመት መጠቀም እንደሚቻል ጭምር የማስጠናት ስራ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል::

የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኦፓል ማዕድኑ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተፈለገ ግዴታ ህጋዊ መሰረት ማስያዝ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ዘውዱ በክልሉ ያለውን ህገ ወጥ የኦፓል ንግድ እንቅስቃሴን በአንፃራዊ መልኩ ይገታል ተብሎ የታሰበውን የኦፓል የግብይት ማዕከል ለመገንባት በጀት ተመድቦ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል::

አሁን ላይ ባለው አለም አቀፍ ገበያ ምንም አይነት እሴት ያልተጨመረበት አንድ ኪሎ ግራም ኦፓል ከ 900 አስከ 1000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጣ ይገመታል፤ በማፅዳትና በመቁረጥ እሴት የተጨመረበት 1 ኪሎ ግራም ኦፓል ደግሞ እስከ 20ሺህ ዶላር ያወጣል የሚሉት አቶ ዘወዱ ማዕድኑ ትልቅ ሀብት ነውና ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፍለግ ይጠቁማሉ::

ከክልሉ ወደ አዲሰ አበባ የሚላከውና ከአዲስ አበባ ወደ ውጭ የሚወጣው ኦፓል መጠኑ የተለያየ መሆኑ በመሀል ተቀንሶ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የሚወጣ ኦፓል እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን የገለፁት አቶ ዘውዱ በግብይት መሀል ያሉትን ደላሎች ለማምከን ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው መወያየትና መስራት እንዳለባቸው ይገልጻሉ::

በአጠቃላይ ከ2008 ዓ.ም አስከ 2010 ዓ.ም ድረስ 10ሺህ 399 ኪሎ ግራም ያልተጣራ ኦፓል ተልኮ 10 ሚሊዬን 632 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል:: እንዲሁም 561 ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረበት የደላንታ ኦፓል ተልኮ 8 ሚሊዬን 767ሺ 944 የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል፤ እንደ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት መስፋፊያ ኤጀንሲ አመታዊ መፅሔት መረጃ :: 
ዘሬ ላይ ማዕድንን በተሸሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚያስችል አዲስ ህግ ወጥቶ በስራ ላይ ለማዋል በእንቅስቃሴ ላይ ነው::

በኩር (ግርማ ሙሉጌታ) ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *