‹‹ካለፉት እና ከጠፋው ንብረት ይልቅ የተጎዳውን የሰውን ሥነ-ልቦና ለማደስ እርቀ ሠላም መፍጠር ይገባል፡፡ › አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው

‹‹ካለፉት እና ከጠፋው ንብረት ይልቅ የተጎዳውን የሰውን ሥነ-ልቦና ለማደስ እርቀ ሠላም መፍጠር ይገባል፡፡ › አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው‹‹ሁላችንም ተሸነፍን፤ ሁላችንም አጣን እንጂ ምንም አላገኘንም፡፡›› ዶክተር አምባቸው መኮንን

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2011ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር የአማራና ቅማንት ሕዝቦች የእርቀ ሠላም መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡ በመድረኩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ምሁራን እንዲሁም ተሳፊዎች ሐሳብ እየሰጡ ነው፡፡የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው ‹‹የተከሰተው እርስ በርስ ግጭት የታሪካችን አንድ ጠባሳ ሁኗል፡፡ የጠፋብንን የሰው ሕይወት፣ ንብረት እና የተጎዳውን የሰው ሥነ-ልቦና መመለስ አለመቻሉ ያመናል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሕይወታቸው ካለፉት እና ከጠፋው ንብረት ይልቅ የተጎዳውን የሰውን ሥነ ልቦና ለማደስ እርቀ ሠላም መፍጠር የማይተካ ሚና አለው፡፡ እርቀ ሠላሙ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው ብሩሕ ሕይወታቸውን ለመመለስ የሚረዳም በመሆኑ ከመጥፎ ታሪካችን መመለስን መጀመር አለብን›› ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት ምንጊዜም የማይረሳ ፀፀት እንደሆነና እንደመሪ እና እንደወገን የሚያሳዝን ድርጊት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ዶክተር አምባቸው ‹‹ባለፈው በተፈጠረው ችግር ካዘንን አሁን ማድረግ የምንችለው ይቅርታ እና ይቅር መባባል ነው፡፡ በሙሉ ልባችን ለሕጻናት፣ ለእናቶች እና ለሴቶች ስንል ልብ ለልብ በመገናኘት የገባብንን ሰይጣን ሕይወታችንን እንዳይነጥቅ ዕድል ልንሰጠው አይገባም›› ብለዋል፡፡‹‹በነብስ ላይ ቁመን መደራደር አይቻልም›› ያሉት ዶክተር አምባቸው ሕይወትን መፍጠር እና ማቆየት የሚቻለው በሠላም ብቻ እንደሆነና ፖለቲካ ከሕይወት ቀጥሎ ዜጎችን ለማሻሻል የሚጥር ርዕዮት በመሆኑ ቅድሚያ ለሠላም ብቻ መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹በዚህ ታላቅ ሀገር አስከፊ የሚባሉት ነገሮች ሁሉ በዚህ ዘመን ታይተዋል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ‹‹ሁላችንም ተሸነፍን፤ ሁላችንም አጣን እንጂ ምንም አላገኘንም›› ብለዋል፡፡ እርቀ ሠላም ሁሉም ሊከተለውና ዋጋም ካለው ሁሉም ሊከፍለው የሚገባው በጎነት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር አዲሱ ገድሉ ለተሳታፊዎች ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጥናት ‹‹እንስሳትን የሚያቃጥል፣ የሰው ልጅ ከእንስሳት ይሻላል ለማለት የማያስችል ድርጊት ፈፅሟል›› ብለዋል፡፡ ወቅቱ እንስሳት ከሰዎች የበለጡበት ጊዜ ይመስል እንደነበርም ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን እርቅን ማምጣት እንደሰው ኅሊና ለመሻሻል ወሳኝ ዕድል ነው፤ አሁንም ለእርቅ አለመመቸት ግን አውሪያዊ ባሕሪ ነው›› ብለዋል፡፡

የእርቀ ሠላሙ ውይይቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ -ከጎንደር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *