ምግባችን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መምሰል ይገባዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 19/2011ዓ.ም (አብመድ) የዓብይ ፆም ሁለት ወራት ለሚጠጉ ጊዜያት ይቆያል፡፡ አሁን ላይ ታዲያ መገባደጃው ላይ ተደርሷል፡፡ እናም ፆሙ ሲፈታ ጥንቃቄ ልንወስድባቸው ከሚገቡ ሥርዓቶች ውስጥ አመጋገባችን ወሳኙን ስፋራ ይይዛል፡፡ ራስን ከስካርና ከሌሎች ፌሽታ ወለድ ምግባሮች መጠበቅና ሌሎች ጥንቃቄዎችን መውሰድም ተገቢ ነው፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የሥነ-ምግብ መምህርት ሐና ደመላሽ ከፆም ወደ ፍስክ ስንሸጋገር ቅባት ወደበዛባቸው ምግቦች እየጣደፍን መሆኑ በመጠቆም የጥንቃቄ መልዕክቶችን ነግረውናል፡፡ በፍጥነት ቅባትነት ወዳላቸው ምግቦች መዛወር ሰውነትን በተለይም ጨጓራን ይከብደዋል፡፡ እናም ቀለል ያሉ እህሎችን በቀዳሚነት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት በባሕላችንም እንደሚደረገው ተልባ ጥቂት ቅቤ ጣል ተደርጎበት ይዘጋጃል፡፡ ይህም በሥነ-ምግብ አስተምሮ የሚመከር መሆኑን ነግረውናል፡፡ ተልባ ብቻ ሳይሆን ሱፍ፣ ሰሊጥና ኑግም ቀለል ያለ ቅባነት ያላቸው ስለሆኑ አስቀድሞ መመገቡ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ የቅባት ዘሮች ለጨጓራ አይከብዱም፤ ስንመገባቸውም ጨጓራን ያለሰልሳሉ፡፡

ቀስ በቀስ እነዚህን ሳንመገብ ሰውነታችን ተላምዶ ከቆየው የምግብ ዓይነት ያለምንም ሽግግር ስጋን አብዝቶ መመገብ ግን ጨጓራ እንዲቆጣ በማድረግ ብቻ ሳይገደብ ተጓዳኝ የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል፡፡ ማስመለስና ተቅማጥ ፆም ሲፈታ ብዙዎችን የሚያጋጥሙ የጤና መታወክ ምልክቶች ናቸው፡፡ ጮማ ከበዛበት ስጋ መቆጠና ቀይ ስጋንም ቢሆን መጠኑን አሳንሶ መመገብ ተገቢ እንደሆነ ከመምህሯ ተብራርቶልናል፡፡ ‹‹በምርምር ተልባ ወይም ኑግ ከተመገብን ከስንት ጊዜ በኋላ ነው ስጋ በትንሹ መውሰድ ያለብን?›› የሚል ጥናት አላገኘሁም፡፡ እንደ ባሕሉና ልማዱ ግን ከአንድና ከሁለት ሰዓት በኋላ በጥቂቱ ስጋን መመገብ እንደሚቻል ይነገራል›› ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የሥነ-ምግብ ትምህርት ክፍል ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር ዑመር ሰይድ ደግሞ ‹‹በፆም ጊዜ የምንወስዳቸው የምግብ ዓይነቶች የቅባትና ፕሮቲን ይዘታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ወደ ፍስክ ስንቀላቀል ተገኘ በሚል ብቻ እንደልብ ከፍተኛ የቅባትና ፕሮቲን ይዘታቸው ከፍ ያሉትን ስንወስድ ከፍተኛ የጤና እክል ያስከትላል›› ነው ያሉት፡፡ ከፍተኛ የቅባትና ፕሮቲን ይዘት ያላቸውን እንደ ስጋ ያሉ ምግቦች በብዙ መጠን መውስድ የኃይል ጫና በሰውነት ውስጥ እንደሚፈጥር ያመለከቱት ረዳት ፕሮፌሰሩ ‹‹ይህም በሰውነታችን ውስጥ በሚያስፈልጉ ነጥረ-ነገሮች ላይ የመዛባት ችግር ያመጣል፣ ቶሎ የመፈጨት ችግር ያስከትላል፤ ከዚያም ሰውነታችን ድርቀት ያጋጥመዋል፤ ሰውነት ፈሳሽ ነገሮችን የሚቆጣጠርበት መንገድ ይዛባል፡፡ ስለዚህ ስጋና የስጋ ተዋፅዖን ስንጠቀም በዝግታና በሂደት በጥቂቱ መሆን አለበት›› ሲሉም መክረዋል፡፡

ወተትም ቢሆን ለረዥም ጊዜ ሳንወስድ ቆይተን በአንድ ጊዜ ብዙ መጠጣት አላስፈላጊ አለመሆኑንም መክረዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራሩም ‹‹ባቆምንባቸው ጊዜያት ወተትን የሚፈጨው ኢንዛይም ሥራውን እያከናወነ አይቆይም፡፡ ስለዚህ በአንድ ጊዜ ብዙ ስንጠጣ ጫና ይፈጠርበትና ከፍተኛ ተቅማጥ ሊከሰት ይችላል፡፡ እናም የሰውነት ፈሳሽ እንዲወጣ አድርጎ እስከህልፈተ ሕይወት የደረሰ አደጋ ሊያደርስ ይችላል›› ነው ያሉት፡፡ በአብዛኛው የጎልማሳ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ይህ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ጠቅሰው በትንሹ መጠጣት ጠቃሚ እንደሆነ መክረዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ሰውነታችን ቅባትን እንዲፈጭ የሚያደረገው ከሀሞት ጋር በተገናኘ ሂደት ነው፡፡ ቅባትነት ያለው ምግብ እንዲፈጭ ከተፈለገ በሀሞት መለስለስ አለበት፡፡ ኬሚካሉ ኢንዛይም እንዲፈጨው ሀሞት ያስፈልጋል፡፡ ከፍተኛ የቅባት ይዘት ካላቸው ምግቦች ለረጅም ጊዜ ርቀን ስንዘልቅ ሀሞትም ከሥራው ርቆ ነው የሚሰነብተው፡፡ ሀሞት ከጉበት መንጭቶ በጉበት ከረጢት ከአንጀት መጥቶ ቅባትነት ያለውን ምግብ እንደ ውኃ እንዲሟሟ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ኢንዛይም መቆራረጥ እንደሚጀምር ምሁራ አስገንዝበዋል፡፡

መምህርት ሐና ደምመላሽና ረዳት ፕሮፌሰር ዑመር ሰይድ እንደ ሥነ-ምግብ ባለሙያ በምክረ-ሐሳባቸው እንደነገሩን ሁል ጊዜም ምግባችን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መምሰል አለበት፡፡ አረንጓዴ አትክልትን፣ ቢጫ ፍራፍሬን፣ ቀይ ደግሞ ስጋን ይወክላሉ፡፡ የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት መዘንጋት የሌለበት የዘወትር ተግባር እንዲሆንም ነው ያሳሰቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *