አጣብቂኝ ዉስጥ ያለዉ የቆዳ እና ሌጦ የንግድ ዘርፍ

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 17/2011ዓ.ም (አብመድ) አቶ ጌትነት ተቀባ በቆዳና ሌጦ የንግድ ዘርፍ የካበተ ልምድ አላቸው፤ ከ20 ዓመታት በላይ በዘርፉ ሠርተዋል፡፡ በባሕር ዳር እና ሞጆ ‹ፍሬንድ ሽፕ የቆዳ ፋብሪካዎች› በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ‹ቤተልሔም ቆዳና ሌጦ አቅራቢ› በሚል መጠሪያ ድርጅት አቋቁመውም ቆዳ ይነግዱ ነበር፡፡ እንዲህ የበዓል ወቅት ሲሆን እስከ 30 ሺህ የበግ፣ የፍየል እና የከብት ቆዳ እና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግን ይህን የሚወዱትንና ለበርካታ ዓመታት የሥራ ልምድ የቀሰሙበትን የንግድ ዘርፍ ለማቆም ወስነዋል፤ በባሕር ዳር የሚገኘው ቤተልሔም ቆዳና ሌጦ አቅራቢ ድርጅት ባለቤት አቶ ጌትነት ተቀባ፡ሌላኛዉ ያነጋገርናቸዉና በደብረ ታቦር ከተማ በቆዳ እና ሌጦ ንግድ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ሙሉጌታ አያሌ የቆዳና ሌጦ ንግድ ልምድን ከአባታቸው ነው የወረሱት፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ አሁን እስካሉበት የጉልምስና የዕድሜ ክልል በዚህ ሥራ ነው የኖሩት፡፡ አሁን ግን የዘርፍ ለውጥ ለማድረግ እያመነቱ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡

ሁለቱም ግለሰቦች ሥራውን ለማቆም ያስገደዳቸው ምክንያት ተመሳሳይ ነው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን እና ከእርድ እስከ ሀገር አቀፍ የግብይት ሂደት ያለው ጥንቃቄ የጎደለው የቆዳ አያያዝ ችግር፡፡ነጋዴዎቹ ጥራቱ የተረጋገጠ እና በገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የቆዳና ሌጦ ውጤት ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡ ይህ ደግሞ ከእርድ በፊት እንስሳቱ በተለያዩ በሽታዎች እንደሚጎዱና በሽታዎቹን ለማከም በባሕላዊ ዘዴ ቆዳቸው ላይ የመብጣት ወይም የመተኮስ ልምድ በአርሶ አደሩ ዘንድ መለመዱ ለጥራት መጓደሉ መንስኤ እንደሆኑም ያስረዳሉ፡፡ጥንቃቄ የጎደለው የእርድ ሥርዓት እና ከነጋዴው እጅ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከማከማቸትና የገበያ ትስስር ለማግኘት እስካለው የማጓጓዝ ሂደት የሚታየው ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝም ሌላኛው የጥራቱ ፈተና ነው፡፡ የጥራት መጓደሉ ደግሞ ዋጋዉን ዝቅተኛ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ለቆዳና ሌጦ የንግድ ሥርዓት ትኩረት መንፈጉን ያሳያሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በነበረው ሂደት መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት የተለያዩ ኬሚካሎችን ያቀርብ ነበር፤ ሽያጭ የሚከናወንበት ቦታ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት ለአቅራቢዎች ልዩ እገዛ ያደርግ ነበር›› ነው ያሉት ነጋዴዎቹ፡፡ የመግዣ ቦታዎችንም ያመቻችላቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ዛሬ ግን ያ ሁሉ ትኩረት ባለመኖሩ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ እነሱም ዘርፉን ለመቀየር እየተገደዱ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ጉዳዩ የሚመለከተው የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲም ከቆዳ ምርት አቅርቦት እና ጥራት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች ከግለሰቦች የዕለት ገቢ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ገዳሙ እንስሳት የጤና እክል ሲገጥማቸው በባሕላዊ ዘዴ አርሶ አደሩ ቆዳቸው ላይ በመብጣት ወይም በመተኮስ የሚሰጠውን ሕክምና ለማስቀረት ዘመናዊ የእንስሳት ሕክምና ማዕከላት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች እየተቋቋሙ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ዳዊት በአማራ ክልል ከሚገኙ 3 ሺህ 453 ቀበሌዎች መካከል በ2ሺህ 419 ቀበሌዎች የእንሰሳት ሕክምና ማዕከላት ተገንብተዉ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በእርድ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ኤጀንሲው ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሁንም የሚታዩ ችግሮች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡ እርዱን የሚያስፈፅሙ፣ እርዱን የሚያከናውኑ እና በቆዳ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ዘርፉ የሚኖረውን ሀገራዊ ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ ማንኛዉም እርድ በቄራዎች እንዲፈጸምም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአማራ ክልል 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን የዳልጋ ከብቶች ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ያለውን ሲሶ የእንስሳት ሀብት ይሸፍናል እንደማለት ነው፡፡ በክልሉ በየዓመቱ 1 ሚሊዮን የከብት ቆዳ፣ 3 ሚሊዮን የበግ እና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የፍየል ሌጦ ይመረታል ተብሎ እንደሚገመትም ከክልሉ እንስሳት ሀብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ክልሉ ካለው የቆዳ ሀብት አንፃር ለገበያ የሚቀርበው የቆዳና ሌጦ ምርት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በሆኑም ከዘርፉ የሚገኘዉን ጥቅም ከፍ ለማደረግ በተለይ በበዓላት ወቅት በሚከናወኑ እርዶች ለቆዳና ሌጦ ምርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ ከእርድ በፊት የእንሰሳቱን ጤና መንከባከብ፣ በእንሰሳት የሕክምና ተቋማት ብቻ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ወደ ገበያም ሆነ ወደ እርድ ቦታ በማጓጓዝ ወቅት እንሰሳቱን በእንክብካቤ ማጓጓዝ፣ በቄራዎች ብቻ እርድ ማከናወን፣ በእርድ ወቅት ቆዳዉ ላይ አጥንት አለ መቀጥቀጥ፣ በአግባቡ መያዝ እና ወዲያዉኑ ወደ ገበያ ማድረስ የዘርፉ ባለሞያዎች የሚመክሯቸዉ የጥንቃቄ መልእክቶች ናቸዉ፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ፎቶ፡- ከድረገጽ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *