ሰሙነ ህማማት ዘሐሙስ (ጸሎተ ሐሙስ)

በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ ማቴ. 26፣ 36-46 ዮሐ.17

#ሕፅበተ_ሐሙስ_ይባላል
ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

#የምስጢር_ቀን_ይባላል
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳስ ሐሙስ ተባለ፡፡

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

ጸሃፊ ዲያቆን ዳንየል ክብረት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *