የተዋሃደው ማንነት!

ይማም አደም ይማም እና ወንድሞቹ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

አደም ይማም አሊ ተወልዶ ያደገው ከደሴ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ኩታበር ነው፡፡ ‹‹ከቀየው የራቀ ሕይወት ይኖረኛል›› ብሎ ባያስብም የሕይወት መንገድ ከ17 ዓመታት በፊት ጀምሮ የከሚሴ ነዋሪ አደረገችው፡፡ ባለቤቱ አሚናት ሙሃመድ ደግሞ ተወልዳ ያደገችው ደዌ ሃረዋ ነው፤ ከሚሴ ገብታ የከተመችውም ገና ልጅ እያለች ከ33 ዓመታት በፊት በ1978 ዓ.ም ነበር፡፡

አደም አማራ ነው፤ የባለቤቱ አሚናት የዘር ሀረግ የሚመዘዘው ደግሞ ከኦሮሞ፡፡ አደምና አሚናት ትዳርን በብሄር ሳይወስኑ ህይዎትን በጋራ ሊኖሩ እና ውጣ ውረድን በጋራ ሊጋፈጡ አደም ‹‹ውሃ አጣጭ›› ያላትን ሚስቱን፤ አሚናት ደግሞ ‹‹አቋራሽ›› ያለችውን የትዳር አጋሯን ካገባች ድፍን 17 ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ በዚህ የ17 ዓመታት የትዳር ቆይታቸውም ከአማራ አባት እና ከኦሮሞ እናት ‹የመጨረሻ ልጅ የሆነውን ይማም አደም ይማምን ጨምሮ ሰባት ኢትዮጵያዊ› ልጆችን ወልደዋል፡፡

በማንነት ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ግጭት የሚያስከትለው የማያባራ ቀውስ እና ጉዳት ምን እንደሚሆን አሰብሁና ሀሳቡን ለአደም አቀረብሁለት። የአደም መልስ ግን ፈጣን ነበር። “እኔ በእነ ይማም አጎቶች እና በአሚናት ወንድሞች ላይ አልተኩስ፤ የአሚናት ወንድሞች በእነ ይማም አባት እና በአሚናት ባለቤት ላይ አይተኩሱ ምን እንሆናለን? የሚገርምህ ምንም እንዳንሆን ሆነን ተጋምደናልና ምንም አንሆንም” አለኝ፡፡

የአደም በራስ መተማመን ልዩ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ ለአሚናት ሳቀርበው ግን ከኦሮሞነቷ ይልቅ እናትነቷ ቀድሞ ‹‹አኡዙቢላሂ በል›› ስትለኝ ‹‹አኡዙቢላሂ›› አልኩ፡፡ ያልኩት ከልቤ ነው፤ ህመሟ ገባኝ፡፡ ይህ ለአሚናት ከሰብዓዊነትም በላይ ነው፡፡ ሰባት ጊዜ ተንበርክካና አምጣ የወለደቻቸው ልጆቿ እንደ ‹‹ሰርገኛ ጤፍ›› የአማራ እና የኦሮሞ የዘር ሀረግ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ናቸውና የእናትነት ህመሟ ገብቶኛል፡፡

ሰሞኑን በአካባቢው የተፈጠረው ችግር ታዲያ መነሻው ምንድን ነው? ስል ለጠየቅሁት ጥያቄ አደም እንዲህ አለ ‹‹የሆነው ነገር ሁሉ እኮ አልገባንም፤ ህዝቡ እኮ ስለተፈጠረው ነገር የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡›› እርግጥ ነው! አለ አደም ‹‹መጀመሪያ ላይ ብዥታ ነበረብን፤ ግጭቱን የብሄርም የእምነትም መልክ ለማስያዝ የተደረገው ጥረት ብዥታ ውስጥ ከትቶን ነበር፤ ነገር ግን የተፈጠረው ችግር የከፋ ጉዳት ሳያደርስ የቆመውም ህዝቡ የድርጊቱ ተባባሪ ስላልነበረ ነው፤ ግጭቱ የአማራ እና የኦሮሞ፤ የእስላምና የክርስቲያን አይደለም፡፡››

ኢስላም ሰላም ነው ያለን አደም ማመን ማለት የሌላውን እምነት ማክበር እንጂ ልዩነትን ማቀንቀን እና መቃቃርን ማወጅ አለመሆኑን ነው የተናገረው፡፡ ወቅቱም አለ አደም ‹‹ከሚሴን ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ ኑሯችን ለማሸነፍ እና ልጅ ለማሳደግ የምንሯሯጥበት እንጂ ዘር የምንቆጥርበት አይደለም፡፡›› ከሚሴ ላይ አማራ እና ኦሮሞ አልተጋጨም፤ ግጭቱ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ነው፤ አደም እንደዚህ ነው የሚያስበው፡፡

የ70 ዓመት የእድሜ ባለፀጋዋ የአደም ይማም አማት እና የአሚናት ሙሃመድ እናት አንሻ አደም አሊን ስለአማራ እና ኦሮሞ አብሮነት ጠየቋቸው እና እንዲህ አሉኝ፣ ‹‹በኖርሁበት እድሜ ሁሉ አማራ እና ኦሮሞ ተባብለን የተለያዬንበትን ጊዜ አይቼና ሰምቼ አላውቅም፤ እድሜ አያሳየው ነገር የለምና አሁን አየሁ፡፡›› ነገር ግን አሉ እናት አንሻ የመጣውን ሁሉ ፈጣሪ በጥበቡ ይመልሰዋል፡፡

ሰላም ለሁሉም!

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከከሚሴ

ፎቶ፦ በመብራቱ ዋለልኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *