ተአምረኛ አተራረፍ በኮንሶ።

⬆️
በዳዊት ዋሲሁን ካሳ

በኮንሶ ከተማ የደረሰብኝ ዝርፊያ፣ ድብደባ፣ እስርና እንግልት በአጭሩ ይህን ይመስላል

በአኪያ ሚዲያ/ፕሮሞሽንና ኢንተርቴይመንት በሰላም ጉዳይ ለምንሰራው ዘገባና ዶክመንተሪ ፊልም ቀረፃ ለማካሄድ ትላንት ወድያ ዕለተ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለኮንሶ ዞኑ ጉዳዩን የሚያሳውቅና ፈቃድ መጠየቅያ ደብዳቤና አስፈላጊ ማቴሪያሎችን ይዤ ኮንሶ ገባሁ።

ሞተር ተከራይቼ ወደ ዞኑ አስተዳደር በመሄድ የስራውን ሁኔታ የሚገልፅ ደብዳቤ በመስጠትና ስለስራው ከዞኑ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ጋዜጠኛ ሰራዊት ከተባለ የተረጋጋና አሪፍ ሰው ጋር ተነጋግረን ፈቅዶልኝ፣ አንድ የዞን ከፍተኛ ባለሞያ መድቦልኝና ለመንቀሳቀሻ የሚሆን ሞተር ሳይክል ሰጥቶን ወጣን።

የዞኑ መንግስትን አሳውቄና ባለሞያ ተመድቦልኝ ቀረፃ አካሄድን። የጎሳ መሪ የሆነው አቶ ገዛኸኝን ኢንተርቪው ስለምናደርገው ወደ መኖሪያ ቤቱ ሄደን ስላጣነው ለአርብ ጠዋት ተቀጣጥረን ተመለስን።

አርብ ጠዋት የተመደበልኝ ባለሞያ እስኪመጣ ካደርኩበት ፔንሲዮን ወጥቼ ቁርስ ልበላ በሞተር ሲሄድ ነው ካሜራ ያዩ ወጣቶች ያስቆሙን።

ወጣቶቹ አስቁመው “ለምንድነው የምትቀርፅው?” አሉኝ። እኔ ሁኔታውን በርጋታ አስረዳኋቸው። ያኔ ነው ወጣቶቹ መሳደብና መዛት ጀመሩ፤ እየበዙም ሆነ። “እኛ ስንበደል በነበር ሰዓት የት ነበራችሁ? ማነው እኛን አድትሰልል የላከህ?” እያሉ ከበው ሊደበድቡኝ ሲቃረቡ አንድ የፖሊስ አባልና ትራፊክ ፖሊስ ደርሰው ወደ ድርጅት ቢሮ ይዘውኝ ሄዱ።

ቢሮ እንደገባን የፈቀዱልኝን የዞኑን ሰዎች ጠራሁ፣ ስለሁኔታ ተነጋገርን። ዞኑ ፈቅዶልኝ እንደሆነ ተማመን። ያኔ እኛ ቢሮ ውስጥ ስናወራ የስራ ሃላፊዎችና ወጣቶች ቢሮን ሞልተውት ነበር። ለዕርድ እንደተዘጋጀ በግ ነበር ያስቀመጡኝ።

“ይህማ የኮንሶን ህዝብ ሊሰልል ነው የመጣው” እያሉ ግርግር ፈጠሩ። የድርጅት ሃላፊውና አንድ ፖሊስ “ላንተ ደህንነት ሲባል ቶሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንውሰድህ” አሉኝ። ፖሊስ ሁኔታውን እኪያመቻች ቢሮ ውስጥ እየገቡ ይሰድቡኝና ይመቱኝ ጀመሩ።

እኔን ለመደብደብ/ለመግደል ከተሰበሰቡት በግምት ወደ 200 የሚሆኑ ወጣቶን በፖሊስ መኪና ታጅቤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄድን። እዛ ስደርስ ቢሮ አስቀምጠውኝ ወጣቱን ሊያረጋጉና የስራ ሃላፊዎች በእኔ ጉዳይ ስብሰባ ሊያደርጉ ሄዱ።

የፖሊስ አዛዡና የመንግስት ሃላፊዎች አድርሰውኝ እንደሄዱ ነው በሌሎች ፖሊሶች ወደ ጣቢያው ታሳሪ ማቆያ ወስደው ድብደባ የፈፀሙብኝና የያዝኩትን ገንዘብ የዘረፉኝ። “አንተ የኮንሶን ህዝብ ልትሰልል የተላክ ነህ” ይሉ ነበር። ሶስት ፖሊሶችና አንድ የደንብ ብልስ ያለበሰ የትራፊክ ፖሊስ አባል ነበሩ የደበደቡኝና የዘረፉኝ።

ደብድበው አልበቃ ሲላቸው ፀጉሬን በመቀስ መሃል ለመሃል አድርገው ቆረጡት። በህይወት ከዛ ቦታ እንደማልወጣ ሲዚቱ ነበር።

በጣም ያሳዘነኝ አንዱ ደብዳቢ ፖሊስ ለታሳሪዎች በኮንስኛ (አንዱ መልካም ሰው እንደተረጎመልኝ) “#ቀጥቅጣችሁ_ግደሉት የኮንሶ ጠላት ነው” ብሎ አሳልፎ ለታሳሪዎች ሰጠኝ። በጣቢያው ያሉት ታሳሪዎች ብዛት ያስፈራ ነበር (በግምት 250 ይሆናሉ)። ያ ሁሉ ይቅርና ለአምስት ሆነው ቢደበድቡኝ ይገሉኝ ነበር።

በሚገርም ሁኔታ አምላክ ትረፍ ሲለኝ አንድ መልካም ሰው በመካከላቸው አለ። እኔን ለድብደባ ወደ ሽንት ቤት አጠገብ እንደሰዱኝ ይህ መልካም ሰው ይመጣና በኮንስኛ ብዙ ከተነጋገራቸው በኋላ ሊደበድቡኝ የነበሩት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ። አንዳንዶችም ያፅናኑኝ ጀመሩ።

እንዳልደበደብ ያደረገው መልካም ሰው አጠገቤ ተቀምጦ ምን እንዳደረኩ ጠይቆ ተረዳ። እኔም ምን ብለሃቸው ነው የተውኝ ስለው “ፖሊሱ ደብድባችሁ ግደሉት” እንዳላቸው እና እሱ ደግሞ “እንዳይደበድቡኝ እንዳሳመናቸው” ነገረኝ።

ቀኑን ሙሉ እዛው ዋልኩ። 10 ሰዓት ሲል የስራ ሃላፊዎችና የፖሊስ አዛዡ መጡና እኔን ከቢሮ ሲያጡኝ ከታሳሪዎች መካከል ይመጡና አገኙን። ተደብድቤ ፀጉሬ ተቆርጦ ሲመለከቱ ደነገጡ። የደበደቡኝንና የዘረፉኝን ፖሊሶች አሳይቼ እንድፈታ አደረጉኝ።

ከተፈታው በኋላም “ወጣቶች ካገኙህ ይገድሉሃልና መኪና ፈልገን ከዚህ ከተማ እንድትወጣ እናደርጋለን” አሉና መኪና ተፈልጎልኝ በህይወት ተርፌ ወጣሁ።

ሶስት የመንግስት ሃላፊዎችና አራት የፖሊስ አባላት እንዲሁ ከታሳሪዎች መካከል ያን መልካም ሰው አምላክ ባያስቀምጥልኝ በህይወት ተርፌ አልወጣም ነበር። አምላክ ይመስገን! የረዳችሁኝ መልካም ሰዎች ከልብ አመሰግናለው!

የሀገሬን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቄ ባውቅም ትላንት የተፈጠረብኝ ነገር ለሀገሬ የማበረክተውን መልካም አስተዋፆ አጠናክሬ እንድቀጥል ያደረገኝ መጥፎ ግን አስተማሪ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

በፖሊስ ጣብያ በነበረኝ ቆይታ የታዘብኩትንና የተነገረኝን አሰቃቂ ግፎች የምፅፍ ይሆናል።

የሚደወልልኝ ስልክና ቴክስት በመብዛቱ መመለስ ባልችልም ለተጨነቃችሁልኝ በሙሉ አመሰግናለው! አምላክ ያክብርልኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *