የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ነው

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2011ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የክልል እና ከተማ አስተዳደር እስልምና ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ የምክር ቤቱ አባላት፣ ዑለማዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች የተካፈሉበትን ጉባኤ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሸህ መሀመድ አሚን ጀማል በንግግር ከፍተዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣይ የሚካሄደው የዑለሞች ጉባኤ ወሳኝ በመሆኑ ለጉባኤው መሳካት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በንግግራቸው አስታውቀዋል።

በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል እና በመላው ሀገሪቱ ያሉትን የእስልምና ልህቀት ማዕከላትን የማጠናከር ሥራ ለነገ የማይባል በመሆኑ ድጋፉ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።

ባለባቸው የጤና ችግር ምክነያት የሥራ መልቀቂያ ማቅረባቸውን ያስታወቁት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ አሚን ጀማል መልቀቂያቸውም ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ ኮሚቴ በቅርቡ በሚያካሂደው ጉባኤ በሚደረሰው ድምዳሜ መሠረት ለሰላምና ለሙስሊሙ አንድነት ሲባል የመጅሊስን አመራር ለመረከብ ዝግጁ የሆነ አካል ካለ የሥራ አስፌፃሚ ኮሚቴው ኃላፊነቱን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን እገልፃለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጉባዔው የተለያዩ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ የሙስሊሙ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ፡- ኤፍ ቢ ሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *