የቻይናዉ ‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ› ለኢትዮጵያ ተስፋ ወይስ ስጋት?

ለሰላም፣ ለትብብር፣ ለግልጽነት፣ አካታችነት እና ለጋራ ጥቅም የሚሉ ዓላማዎችም ነበሩት፡፡ ‹‹ዘ ሲልክ ሮድ›› ለቻይናዉያን የጥንት ብልጽግናቸዉ እና ክብራቸዉ ትዝታ ነዉ፡፡እናም የቀድሞ ክብሯን የሚመልስ፣ አሁን ያላትን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያረጋግጥና የሚያስቀጥልም የ21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ግዙፍ ፕሮጀክት ሆኖ ተነደፈ፤ ‹ዋን ቤልት ዋን ሮድ›፡፡ የቀጣይ 50 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ፕሮጀክትም ነዉ፡፡ የቀድሞዉ ‹ዩሮዢያ› (የአውሮፓ-እስያ) ኃያልነት መገለጫ የንግድ ትስስር ትልም ‹‹ዘ ሲልክ ሮድ›› ዳግም ትንሳኤ ብስራት ወቅቱ መስከረም ወር 2013 (እ.አ.አ) ነው፤ በጊዜው የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ዢ ቺፒንግ ካዛኪሰታን ናዛርባየቭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተዉ ስለ ‹‹ዋን ቤልት ሮድ ኢኒሸቲቭ›› ፕሮጀክት ዕቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር አደረጉ፤ በዚያዉ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ኢንዶኔዥያ ፓርላማ ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግርም ስለ ‹‹ዋን ቤልት ሮድ›› ፕሮጀክት ዕቅዳቸዉ ይፋ አደረጉ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የቻይና ባለስልጣናት በዓለም የነዳጅ ላኪ ሀገራት ኅብረት (ኦፔክ) እና የቡድን-20 ሀገራት ጉባኤ ላይ ጭምር ጉዳዩን አጀንዳ ያደረጉት፤ ዋን ቤልት ዋን ሮድ ኢኒሸቲቭን፡፡

ፕሮጀክቱ ከ4 እስከ 8 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመት ነው። አውሮፓንና እስያን ማዕከል አድርጎ በአፍሪካና ሌሎች አህጉሮች የሚገኙ ሀገራትን በየብስና በውኃ ትራንስፖርት ጨምሮ በዘርፈ ብዙ መሠረተ ልማቶች ለማስተሳሰር የተነደፈ ዕቅድ ነው። ዋነኛ ዓላማው ደግሞ በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ ነው። እስካሁን ድረስ የትብብር ማዕቀፉን ሰነድ በመቀበል ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 አገሮችና 29 ዓለም አቀፍ ተቋማት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ‹‹የጋራ የሆነውን ብሩህ መጪ ጊዜ መሥራት›› በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው እና ከ40 በላይ የሚሆኑ አገራት መሪዎች በታደሙበት የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባዔ ላይ ለመሳተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በቻይና ስኬታማ የሚባል ቆይታ እንዳደረጉ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በክትትል መረጃዉ ገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የልዑካን ቡድን በቻይና ቆይታው የብድር ወለድን ማሰረዝንና የአዲስ አበባን ማስዋብ ፕሮጀክት ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ስምምነቶችን አድርጓል፡፡
ዋን ቤልት ዋን ሮድ ኢኒሸቲቭ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ከሆነ ጀምሮ በአዎንታዊም፣ በአሉታዊም መልኩ ብዙ እየተባለለት ይገኛል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰሩ ዳዊት ሀዬሶ (ዶክተር) ስለ ፕሮጀክቱ ከአብመድ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ስጋቶቹንና ተስፋዎቹን አንስተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ጉዳዩን ቻይና ከኢትዮጵያ ብሎም ከቀጠናዉ ሀገራት ጋር ካላት ግንኙነት እና ከምትከተለዉ ስትራቴጂ አንጻር መዝነውታል፡፡ ቻይናዊዉ ‹‹የዋን ቤልት ዋን ሮድ›› ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ለሚተገበሩ የልማት ሥራዎች አማራጭ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት እምነት አላቸው። በዚህም ሰፊ የገበያ እና የኢንቨስትመንት አማራጭ ባለዉ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የመሠረተ ልማት ዝርጋታን መደገፍ ቀጠናዉን በገበያ ለማስተሳሰርና የኅብረተሰቡ ዕድገት ለማሳለጥ አዎንታዊ ድርሻ እንደሚያበረክት እና የጋራ ጠቀሜታ እንዳለዉም ገልጸዋል፡፡ ሀገራቱን ብሎም አህጉራቱን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር የንግድ፣ የቴክኖሎጅ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ያቀላጥፋል ያጠናክራልም ባይ ናቸዉ፡፡ የኢትዮ ቻይና ግንኙነት ረጅም ጊዜ ዕድሜ ያለዉ እና በሁሉም ዘርፍ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ የቀጠናዉን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር መደገፍ ዓላማ አድርጎ ከሚሰራዉ ኢጋድ ዉስጥ ኢትዮጵያ የምትጫወተዉን የጎላ ሚና ያጠናክራልም ብለዋል፡፡

በተለይ ኋላ ቀር የመሠረተ ልማት አዉታር ባለባቸዉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አፍሪካ ሀገራት ከችግሩ ለመዉጣት የሚያደርጉትን ጥረት ያበረታታል፡፡ ምቹ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለ ማለት የገበያ ትስስሩ ይፋጠናል፣ ምርትን በሚፈለገዉ ጊዜ፣ ቦታና መጠን ወደ ገበያ ማቅረብ ያስችላል፡፡ ባለሀብቱ ኢንቨስት ለማድረግ ከሚያቀርባቸዉ መስፈርቶች መካከል ምቹ መሠረተ ልማት አንዱ ነዉ፡፡ ይህ ፕሮጀክት ደግሞ ሀገራቱን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር በመሆኑ የዉጭ ኢንቨስትመንቱን እንዲበረታታ ያደርጋል፤ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ 
ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት በዚህ ፕሮጀክ ማዕቀፍ ዉስጥ በቻይና የገንዘብ ድጋፍ ከተከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል በምሥራቅ አፍሪካዋ ኬንያ በ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከሞምባሳ ናይሮቢ የተዘረጋን የባቡር መስመር በምሳነት ጠቅሰዋል፡፡ የባቡር መስመሩ 12 ሰዓታት ይፈጅ የነበረዉን ጉዞ ወደ 4፡30 ማሳጠሩ ፈጣን የገበያ ትስስር፣ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር እና የዕቃ ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ 752 ነጥብ 70 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለዉን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር 95 በመቶ የዉጭ ንግዷን በጅቡቲ መስመር ለምታከናዉነዉ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አካል እንደሆነ አንስተው ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ሦስት ቀናት ይፈጅ የነበረዉን ጉዞ ወደ 12፡00 አሳጥሮታል፡፡ ይህ ደግሞ የገቢና ወጭ ንግዱ የተሳለጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በመሆኑም በብዙ መልኩ ሲታይ ፕሮጀክቱ መልካም ተስፋዎቹ ያመዝናሉ ብለዋል ምሁሩ፡፡

ነገር ግን ስጋቶች የሉትም ማለት እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡ ለአብነት በማዕቀፉ የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ትላልቅ በመሆናቸዉ ከፍተኛ በጀት የሚመደብላቸዉ በመሆኑ ለሙስና የተጋለጡ ናቸዉ፣ ገንዘቡ በብድር የሚገኝ በመሆኑ የፕሮጀከቶቹ አዋጪነት በአግባቡ ካልተጠና፣ በወቅቱ ተጠናቅቆ መስጠት ያለበትን አገልግሎት መስጠት ካልጀመረ ተጨማሪ ዕዳ ነዉና ሀገራት መክፈል በማይችሉት ዕዳ ዉስጥ እንዲዘፈቁ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሰለሞን መብሬ (ዶክተር) ደግሞ ‹‹ወቅቱ ሉላዊነት የተንሰራፋበት የበይነ መረጃ ዘመን መሆኑ ግንኙነቱን አይቀሬ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡ በዚህ ዘመን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ የባሕል ዉርርስ እና የልማት ትብብር እያደገ የሚመጣበት መሆኑን መረዳት ይጠይቃል›› ብለዋል፡፡ የኢትዮ-ቻይንና ግንኙነት የቆየና እያደገ የመጣ መሆኑን አዉስተዉ ወደ ፊት በጥናት የሚረጋገጥ ቢሆንም አዎንታዊ ጎኖቹ እንደሚያመዝኑ ተናረዋል፡፡

ስጋቶች መኖራቸውን የተጋሩት ዶክተር ሰሎሞን ስጋቶቹን ለመቀነስ የሀገር ጥቅም እና ክብርን በሚያስጠብቅ፣ ሕጋዊ በሆነ መልኩ፣ ሁሉን በማያጠራጠር በዕዉቀት ላይ የተመሠረተ አቅራቢ የሆነ ግንኙነት እንዲሆን መሥራት ይጠይቃል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረዉ አለመረጋጋት ኢኮኖሚዉን ጎድቶታል›› ያሉት ምሁሩ በማዕቀፉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እዉን በማድረግ እንዲያንሠራራ ማድረግ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡

የረጅም ጊዜ ተጽእኖችን ማጥናት፣ ፖለቲካዊ እዉነቶችን ማጣጣም፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚጠይቅም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡ የፕሮጀክቶች ስምምነት እና አተገባበር ግልጽ እና ሕዝብን ያሳተፉ እንዲሆኑ ማድረግ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጥንታዊዉ የታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ እንዳለዉ ፐርሺያዎች ለዉጭ ግንኙነት ራሳቸዉን ክፍት አድርገዉ አዳዲስ አስተሳሰብና ስልጣኔን የመቀበል ዝንባሌያቸዉ ስልጡን እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፤ እናስ ይህ ቻይናዊ የትስስር ፕሮጀከት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዉ ባለፈ ለየት ያለ ሰፋ ያለ እሳቤን ይዞልን ይመጣ ይሆን ወይስ …?

ተጨማሪ የመረጃ ምንጮች፡- ሲ ጂ ቲ ኤን፣ ዘ ሲልክ ሮድ ኤ ኒዉ ሂስትሪ ኦፍ ዘ ዎርልድ መጽሐፍ

ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸዉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *