የማላዊ ሐይቅን ሙሉ በሙሉ በዋና ያዳረሰው ሰው በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ሰፈረ

የማላዊ ሐይቅን ሙሉ በሙሉ በዋና ያዳረሰው ሰው በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ሰፈረ፡፡ ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 19/2011ዓ.ም (አብመድ) አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ከ580 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት በማላዊ ሐይቅ ላይ በመዋኘት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡ ሐይቁን ከዳር እስከ ዳር በዋና የዘለቀው ማርቲን ሆብስ 54 ቀናትን ፈጅቶበታል፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት በጀርባ ሕመም ምክንያት ከማራቶን ሩጫና የጎዳና የብስክሌት ውድድር ራሱን ያገለለው ሆብስ የማላዊ ሐይቅን ሙሉ በሙሉ በዋና በመሸፈን የመጀመሪያው ሰው ሆኗል፤ ለረዥም ጊዜ በመዋኘትም በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል፡፡

‹‹በአፍሪካ ምድር አንድ ተዓምር መሥራት እፈልግ ነበር፤ በዓለም ላይ የሚያሳውቀኝና የሚያስታውሰኝ ታሪክ ሳልሠራ እንዳልሞት እፈራ ነበር፤ አሁን ተሳክቶልኛል፤ ከእንግዲህ ታሪክ አለኝ›› ብሏል፡፡የማላዊ ሐይቅ እንደ ጉማሬና አዞ ያሉ አደገኛ እንስሳት ያሉበት ነው፡፡ ሆብስ ስለ 54 ቀናት ቆይታው ሲናገርም ‹‹በሕይወቴ ረዥሙን የውኃ ላይ ጉዞ ነው ያደረግሁት፤ የማልደብቃችሁ ነገር ቢኖር አዞዎችን በጣም እፈራ እንደነበር ነው›› ብሏል፡፡

በየቀኑ በአማካይ ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ ይዋኝ እንደነበር የገለጸው ሆብስ ስኬቱን በደቡብ አፍሪካ ለሚገኝና የፊት ገጽታ ችግር ላለባቸው ሕጻናት መርጃድርጅት ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚጠቀምበት አስታውቋል፡፡

ምንጭ፡- ዩ ፒ አይ

በአብርሃም በዕውቀት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *