የእንጅባራ ነዋሪዎች የአደንዛዥ ዕፅ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ተናገሩ

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 18/2011ዓ.ም (አብመድ) የወጣቶችን ስብዕና የሚጎዱ የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያ ቤቶች መበራከት እንዳሳሰባቸው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ነዋሪዎች በከተማዋ የጫት፣ የሽሻና መሰል አደንዛዥ ዕፆች እየተበራከቱ ቢሆንም ከመንግሥት አካላት የሚሰጠዉ ትኩረት አናሳ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ስማቸዉ እንዳይጠቀሰ የፈለጉ ነዋሪዎች ለአብመድ እንደጠቆሙት የአደንዛዠ ዕፅ በወጣቶች ስብዕናና ጤና ላይ እያደረሰ ካለዉ ጉዳት ባሻገር የሌቦችና የወንጀለኞች መሸሸጊያ እየሆነም ነዉ፡፡ የሚመለከተዉ አካል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል፡፡የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኤንስፔክተር ያዛቸዉ መንግሥት ‹‹በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ንብረታቸዉን ከመዉስድና ከማስተማር ዉጭ የእርምት እርምጃ ለመዉሰድ የሚያስችል የሕግ አግባብ አለመኖር ችግሩ እንዲባባስ አድርጐታል›› ብለዋል፡፡

በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላትን በማስተማርና የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎችን የማቃጠል ሥራ በተደጋጋሚ እየተሠራ ቢሆንም ችግሩን መቅረፍ እንዳተቻለ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በከተማዉ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 18 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች መያዛቸዉንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *